ዋ እንግሊዝ የሥልጣኔዋ አውራ፤ ዐየኋት ስትመክን በታሪኳ አፍራ! ==================================
የአንድን ማኅበረሰብ የጀግንነት ታሪክ እየኮነኑ ትውልዱን መጋት፤ ለጥፋትና ሞቱ የጦር ዘመቻ ሳያስፈልግ ራሱን በራሱ፣ ልቡን በምላሱ የሚሰልብበትን፣ የሚያጠፋበትን ካራ መስጠት ነው!
ዛሬ የምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ ፋና ወጊ የነበረችው እንግሊዝ፣ በገዛ ታሪኳ እንድታፍርና እንድትሸማቀቅ በተደረገ ስልታዊ “የትርክት ክለሳ” ወኔዋ ተሰልቦ በመመከን ላይ ትገኛለች።
ትናንት ሀገር ያቀኑ፣ ግዛት ያስፋፉና ዓለምን የለወጡ አርበኛ እንግሊዛውያን (እንደ ዊንስተን ቸርችል፣ ወይም ቪክቶሪያዊያኑ መሐንዲሶች) ዛሬ በትምህርት ቤቶችና በሚዲያ የሚቀርቡት እንደ ጀግና ሳይኾን እንደ “ጨቋኝና ዘረኛ” ተደርገው ነው።
የቸርችል ሐውልት ሲቆሽሽ፣ የጀግኖቹ ስም ከታሪክ ገጽ እንዲጠፋ ሲደረግ፣ ትውልዱ የሚቀበለው መልእክት “የአባቶቼ ታሪክ የውርደት ነው” የሚል ነው። የትናንትን ታሪክ በዛሬ መነጽር እያዩ ፍርድ ለመስጠት መጣደፍ፤ ነገ ትውልድ የሚገነባበትን መሠረት ማሳጣት እንዳይኾን ከስሜታዊነት የራቀ ልባዊነትን ይሻል።
አለበለዚያ ግን በትውልዱ ውስጥ የነበረውን የጀግንነት ወኔ ሰልቦ፣ በምትኩ የጆርጅ ፍሎይድ ስም በተጠራ፣ ብላክ ላይቭስ ማተር በተነሳ ቁጥር ሁልጊዜ ይቅርታ የሚጠይቅና የሚሸማቀቅ እንከፍ ይፈጥራል።
ስለኾነም ትውልዱ ስለ ሀገሩ ክብር፣ ስለ ዜጎቹ መብት፣ ፍትሕና ሉዓላዊነትም እንዳይሟገት በታሪክ ጥፋተኝነት ሰንሰለት ታስሮና ተሸብቦ ይኖራል።
በዚያም የራሱን እሴትና ባሕል ለማስከበር፣ ወግና ልማዱን ለማስቀጠል፣ እምነትና አምልኮውን ለመፈጸም ድፍረት አጥቷል፤ ምክንያቱም ስለ ጀግንነትና ስለ ሀገር ፍቅር ማውራት እንደ “ኋላቀርነት” እንዲቆጠር ተደርጓልና።
ይህ ዛሬ አሁን ይህንን በምጽፍላችሁ የ2018 ዓ.ም. በተጋመሰ በሁለተኛው መንፈቅ በመጋቢትም ወር እየኾነ ያለ አሁናዊ ሐቅ ነው።
ወኔ-ቢስነት ትውልዱን(የእንግሊዝን ወጣት) ለኑሮ ከሚታጠቀው ድፍረት ለይቶታል። ሳይዋጋ የተሸነፈና ሳይሟገት የተረታ ትውልድ ደግሞ ለባዕዳን ትርክትና ለባህላቸውም የበላይነት የተመቸ ባርያ ይኾናል፤ ኾኗልም።
የጀግንነት እሴት ሲሰልብ፣ የክብር ታሪክ ሲንቋሸሽ የወንድነትና የአባትነት ኃላፊነትም አብሮ ይሰለባል፤ ይጠፋልም። ለሀገርና ለክብር የመሞት ወኔ የሌለው ትውልድ፣ ለቤተሰብና ለትዳር፣ ለማኅበረሰብና ለትውልድ መስዋዕት የመኾን አቅም ፍላጎትም የሌለው ራስ ወዳድና ደካማ ኾኖ ይወጣል።
ልክ እንደ ጃፓኖቹ ሁሉ ተስፋ የቆረጠ፣ የማያገባ፣ ቢያገባም የሚፋታ፣ የማያረግዝ፣ ቢያረግዝም የሚያስወርድ እንጂ የማይወልድ፣ የማይዋለድ ትውልድ በዛሬዋ እንግሊዝ የበዛው ለዚህ ነው።
የቤተሰብ መፈራረሱና የብቸኝነት ወረርሽኙ የዚሁ የመንፈስ ስብራት ውጤቶች ናቸው። ትናንትናውን፣ ታሪኩን፣ እሴቱን እንዲጠላ፤ የአባቶቹንም ጀግንነት እንዲያንቋሽሽ ተደርጎ ያደገው ትውልዱ፤ ስለ ነገው ተስፋ የሌለውና ለራሱም ክብር የማይሰጥ መኾኑ፣ ሀገሪቱ በቁጥርም በመንፈስም ትውልድ አልባ ኾና እንድትመክን አድርጓታል።
ጥቃቅን ስህተቶችን በማጉላትና ታላላቅ ስኬቶችን በማጥቆር በጠላትና በቅጥረኛ ምንደኛ ሊቃውንቱ የሚጻፈው ትርክት፣ እንግሊዛዊውን በገዛ ሀገሩ እንደ ባዕድ እንዲሰማው አድርጎታል።
በዚያም ከራሱ ልጆች፣ ሕጎች፣ እሴቶች፣ ወጎች ይልቅ ባዕዳንን፣ ስደተኞችንና እሴቶቻቸውን ወጎቻቸውን በራሱ ደምና ወዝ የሚጠበቅ፣ የሚያስጠብቅ ኾናል! የራስ ጠልነቱ ጥግም ከዚህ አድርሶታል!
የታሪክ ጸሐፊው ራሱ ለሚገፋው ማርክሳዊ ርዕዮተ-ዓለም አገልጋይ ኾኖ የጥንት ጀግኖችን ሲያጠቃ፣ ትውልዱ የሚማረው ታሪክን ሳይኾን በደለኝነትን፣ ጥፋተኝነትን ነው።
ጃፓንና እንግሊዝ በራሳቸው ሆዳደር ሊቃውንቱ የተከለሰ ታሪካቸው የሰለባቸው ወኔ-ቢስ፣ ልባልባ ኾነው የቀሩት በዚህ ሂደት ነው።
ኢትዮጵያ ጋር ገና አልደረስኩም የተሰራብን ሸፍጥ፤ በተለይ ለማምለክ ጥቂት እስኪቀረን ድረስ ባቆለጳጰስናቸው ሊቃውንትና ተቋማት የተሸረበብን ሴራ እንዲገባን ሌላ አንድ አርበኛ የነበረችን ሀገር ደግሞ ጎብኝተን እንምጣ!
ይህ የአባወራው ንቅናቄ ነው!
ወንዱን ወደ ልብ አባወራውን ወደ ግርማና ክብሩ የሚመልስ!💪
(ጽሑፎቹ እንደተለመደው በስልኬ ላይ በችኮላ ስለሚጻፉ እያቃናችሁ አንብቧቸው)


